የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የጤና ስረአቷ ደካማ ለሆነው ሀገር ተስፋ ይሆን ፤ ይሆን?
ጤና ይስጥልን የተከበራችሁ የዝግጅታችን ተከታታዮች እንደምን አላችሁ? በዛሬው ዝግጅታችን ኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች 10 ዓመት ያስቆጠረውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት በሀገሪቱ የጤን አገልግሎት ስረአት ይዞት የመጣውን ተስፋ እና በሂደት የገጠመውን ተግዳሮት በአጭሩ እናስቃኛለን ። መንግስት ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት በተጨማሪ የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎች የማህበራዊ ጤና መድህን የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ የሚያደርግ የመድህን አገልግሎት ለመጀመር በህግ ማዕቀፍ የታገዘ ዝግጅት ስለማድረጉም ሰምተናል። አብራችሁን ከቆያችሁ የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች አስተያየት ጨምሮ አገልግሎት አቅራቢዎችን እና ሌሎች ባለድርሻዎችን ያነጋገርንበትን ዝግጅት ታደምጣላችሁ ፤ታምራት ዲንሳ ነኝ ።
የህብረተሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎትን ለዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀችው ጀርመን ስትሆን ጊዜውን እንደ ጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር 1883 ነበር ። በጀርመን ከ140 ዓመታት ግድም የደረሰው የማህበራዊ ጤና መድን አገልግሎት ሀገሪቱን አሁን ከዓለማችን ቀዳሚ ፣ ጥብቅ እና የተሻለ አገልግሎት የሚያሰጥ የጤና ስረዓት ካላቸው ቀዳሚ ሀገራት ውስጥ እንድትገኝ አስችሏታል። በጀርመን የመኖሪያ ፈቃድ ያገኘ ማንኛውም ሰው በዚሁ የጤና መድህን አገልግሎት መታቀፍ ግድ ይለዋል። ይህ ደግሞ በየትኛውም የኑሮ ,ረጃ ላይ የሚገኝ ግለሰብ በሀገሪቱ እጅግ ውድ በሆነው የጤና አገልግሎት ስረዓት ውስጥ ያለችግር የተሟላ የጤና አገልግሎት እያገኘ እንዲኖር አስችሎታል። የተከበራችሁ የዝግጅታችን ተከታታዮች ይህን ያለምክንያት አላነሳንም ። በኢትዮጵያ ተቋቁሞ 10 ዓመታትን ያስቆጠረው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ከተነሳለት ዓላማ እና ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ በቁንጽልም ቢሆን ለመቃኘት እንሞክራለን። ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ የኢትዮጵያ ጤና መ,ድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ናቸው ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የማህበራዊ የጤና መድን አገልግሎት ከተወሰደ ተሞክሮ በመነሳት በኢትዮጵያ ሁለት አይነት የጤና መድን አገልግሎት ለመስጠት ታሳቢ በማድረግ መጀመሩን ያስታውሳሉ።
ማህበራዊ የጤና መድን ዋስትና የገጠመው ችግር
የጤና አገልግሎት ሽፋን መስፋፋት ለአገሪቱ የተቀላጠፈ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ማኅበራዊ የጤና መድን አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ አዋጅ አውጥታለች።
የጤና መድን ዋስትና
በዚሁ አዋጅ 690/2002 መሰረት፣ በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ ሶስት ዓይነት የጤና መድን ዋስትና(ኢንሹራንስ) አገልግሎት ስርዓት አሉ። ከሶስቱ አንዱ የሆነው ሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሰራተኞችን እና የጡረታ ባለመብቶችንም እንዲያቅፍ የተዘጋጀው ማህበራዊ የጤና መድን ሽፋን ነው። ሌሎቹ የግል እና የማህበረሰባዊ የጤና መድን አገልግሎቶች ናቸው። በኢትዮጵያ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ማኅበራዊ የጤና መድን አገልግሎት እክል እንዳጋጠሙት ተነግሮዋል። ይኸው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሊጀመር የታሰበው እና ግዴታን መሰረት ያደረገው ማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በስራ ላይ መዋል የነበረበት።
«በእኛ አቆጣጠር በ2004 እና 2003 አካባቢ ተርጾ ሁለቱ አይነት የጤና መድህን በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ለመጀመር አንደኛ ማሕበራዊ ጤና መድን የሚባል የሚባል ፤ ደሞዝ ተከፋይ እና ጡረተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ማህበራዊ የጤና መድህን የምንለው እና ሌላው አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ወይም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን እንዲኖር ነበር እንደሀገር የተቀረጸው።»
በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል የሚኖረው በገጠር እንደመሆኑ እና አርሶ አደር ፣ አርብቶአደር አልያም በሌላ ኢመደበኛ በሆኑ ሌሎች የስራ መስኮች የተሰማራ የህብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑ ለትግበራ ቅድሚያ ያገኘው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ነው። በኦሮሚያ ፣ አማራ ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች በተመረጡ ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው አገልግሎቱ አሁን እስከ 45 ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን በአገልግሎቱ ተደራሽ ማድረጉን ወ/ሮ ፍሬህይወት ይናገራሉ።

«በእኛ ሀገር ውስጥ ባለው ሁኔታ ወ,ደ 894 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እያደረግን ነው። በእነዚህ ወረዳዎች አሁን ባለው ሁኔታ አባልነት በቤተሰብ ደረጃ ነው። በዚህም 45 ሚሊዮን ተጠቃሚ አለን።»
በእርግጥ ነው ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሃገራት ቀርቶ በኤኮኖሚ ባደጉ ሃገራትም ጭምር ለጤና አገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያ ወደ ማይቀመስበት ደረጃ እየደረሰ ነው። አገልግሎቱ እንዲህ በመድህን ዋስትና ሲታቀፍ ይብዛም ይነስ እፎይታ ማስገኘቱ አልቀርም።
ነዋሪነታቸውን በምዕራብ ጎጃም ዞን ኤልማና ዴንሳ ወረዳ መሶቦ ቀበሌ ያደረጉት አቶ ስንታየሁ ሁነኛው ውቤ ከቀበሌያቸው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎትን ቀድመው ካገኙት አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው ። ቀደም ሲል የጤና አገልግሎት ለማግኘት ይገጥማቸው የነበረውን እና አባልከሆኑ በኋላ በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ካዩት አካፍለውናል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ዋስትና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት ሌላው ነዋሪነታቸውን በጅማ ዞን ያደረጉ አርሶ አደር የመድህን አገልግሎቱ ይዞላቸው የመጣውን ገጸ በረከት እና የገጠማቸውን ችግር ይናገራሉ።
«በበቀደሙ የአረፋ በዓል መጥቼ ቀዶ ህክምና ተደረገለኝ። ብዙ ገንዘብ አውጥቼ መታከም የማልችለውን ይኸው በነጻ ታክሜአለሁ። ከውች የገዛሁት ሄዴ ውስጥ የታጠበበትን ጉሉኮስ ብቻ ነው። ፈሳሹ እዚህ ሲታጣ አንዱን ከውጭ ፋርማሲ በ300 ብር ገዝቻለሁ።»
ሌላ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ጅማ ሆስፒታል ውስጥ እየታከሙ በስልክ ያነጋገርናቸው አርሶአደርም እንዲሁ ተመሳሳይ ሃሳብ አካፍለውናል።
«እዚህ ስንመጣ በደንብ ተቀብለውናል። በተኛንበት መጥተው ህክምና ሰጥተውናል። መርፌም አግኝንተናል። ነገር ግን የመድሃኒት ግዢ ብቻ ነው ችግራችን ። እስከ ሁለት ሺ ፣ ሶስት ሺ ብር ድረስ የሚያስወጣን የፋርማሲ መድሃኒት ግዢ ነው። »
ማህበራዊ የጤና መድን በኢትዮጵያ
ማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓትን በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ በ2002 ዓ/ም አዋጅ ወጥቶለትና መዋቅር ተዘጋጅቶለት ነበር። ግን ሥርዓቱ በገጠሙት አንዳንድ ችግሮች የተነሳ እስከአሁን ስራ ላይ አልዋለም።
4:11 min
የጤና መዲን
ምክንያቱንም ለማወቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጥቂት ጊዜ በፊት የተሾሙትን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን ሐሙስ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ምክር ቤቱ ጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቁ ይታወቃል።
ሥርዓቱ እስካሁን ተግባራዊ ያልሆነው «በቂ ቅድመ ዝግጅት ስላልተደረገለት፣ የሠራተኞች ግንዛቤ አናሳ ስለሆነና የመድኃኒት አቅርቦትና ከጤና ተቋማት አካባቢ እንከኖች ስላጋጠሙት» ነዉ ሲሉ ሚንስትሩ አስረድተው፣ ሥርዓቱ ምናልባት በሌላ ሊተካ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ሌላዉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የሚባለዉ በገጠር ያሉት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ለመጥቀም የታሰበ ሲሆን በሙከራ ፕሮከክት ከ18 ሚልዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን በጤና ጥበቃ ሚንስቴር የህዝብ ግኑኙነትና የኮሙኒኬሼን ዳይሬክቴር አቶ አህሜድ ኢማኖ ይናገራሉ። ይህም መድን ከዚህ ዓመት ጀምሮ፣ አዋጅ ወጥቶለት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ስራ ላይ መዋል እንደሚጀመር ዳይሬክቴሩ ጠቅሰዋል።
በአገሪቱ ያሉት የመድን ድርጅቶች ለተወሰኑ ሰዎች የጤና መድን አገልግሎት ቢሰጡም ወደ 100 ሚሊዮን ህዝብ ያለበት አገር ዉስጥ የነሱ አገልግሎት ብዙም ትርጉም እንደሌለዉ የጤና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ይገረሙ አበበ ለዶቼ ቬሌ ገልጸዋል። ለዚህም መንግስት ሁለት አይነት መድኖችን ማለትም፣ ማኅበራዊ የጤና መድንና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ቢመሰርትም «መጨረሻ ላይ ሁለቱም ተዋህዶ አንድ አገራዊ መድን» እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር ይላሉ ደክተር ይገረሙ። የማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓት እስካሁን ስራ ላይ እንዳይዉል ያሰናከሉ ሌሎች ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ነው ዶክተር ይገረሙ ያስረዱት።
አገሪቱ በጤና ዘርፍ ፕሮግራሟን ለማስፈፀም በአብዛኛዉ የዉጭ ርዳታ ላይ ጥገኛ እንደሆነች እና ይህም በዚህ መልክ ሊቀጥል እንደማይችል የሚናገሩት ደክተር ይገረሙ ማኅበራዊ የጤና መድን ሥርዓትን ማስተዋወቅ በጣም ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።
የጤና መድህን ዋስትናው በእርግጥ በዝቅተና የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው እና በቁጥር ከፍተኛውን ደረጃ ለሚይዘው የህብረተሰብ ክፍል አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው አይታበልም። ተጠቃሚዎቹ ከሚናገሩት መረዳት እንደተቻለው ቀደም ሲል ከነበረው ራስን ችሎ የህክምና አገልግሎት ከማግኘት አንጻር አንድ እርምጃ የተራመደ ይመስላል።
ነገር ግን የመድህን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ አላማዬ ብሎ ይዞ ከተነሳው እና ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል ለማገለገል ለወትሮም ቢሆን የአቅርቦት ችግር ውስጥ ያሉት የመንግስት የጤና ተቋማት ፤ ዉሉን መሰረት ያደረገ ስራ ለመስራት አቅም አንሷቸዋል፤ አልያም ብርቱ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል።
በጅማ ዞን ዴዶ ወረዳ የሚገኘውን የመንግስት ሆስፒታል በሃላፊነት የሚመሩት አቶ አወል መሀመድ እንደሚሉት ሆስፒታላቸው ለማህበረሰብ አቀፍ የመድህን አገልግሎት አባላት የተገባውን ውል መሰረት ያደረገ ያደረገ አገልግሎት ለማቅረብ የፋይናንስ አቅርቦት ፈታኝ ሆኖባቸዋል።

የጤና መድህን አ,ገልግሎቱን እየገጠመ ባለው የአቅርቦት ችግር ላይ ከተጠቃሚዎች እና ከባለ ድርሻ አካላት በቀረበው ቅሬታ ላይ እንደሚስማሙ የሚናገሩት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ ከክልል አስተዳደሮች ጋር በመተባበር የማህበረሰብ የመድሃኒት መደብሮችን ወይም ፋርማሲዎችን እያስፋፉ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው ያንኑ የመክፈል አቅም አጥተው የሚቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ማድረጉ ሌላው ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ ነው። በእርግጥ ሁሉን ነገር ለመንግስት መተው አይገባም የሚሉት በአበባ ልማት እና ሌሎች የአስመጭ እና ላኪ የንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ጸጋዬ አበበ በሁለት ዓመት ውስጥ ከ800 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ይህንኑ የመድህን ዋስትና መግዛታቸው ይናገራሉ።
መሰል ማህበራዊ ችግሮችን በማቅለል ረገድ ሚና ያላቸው የመድን ዋስትናዎች ለሀገሪቱ አንዳች ተስፋ ስለመሰነቃቸውም ጭምር ነው አቶ ጸጋዬ የሚናገሩት ።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሁን የማህበራዊ ጤና አገልግሎት ወይም የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ በመደበኛ የስራ መስክ ላይ የተሰማሩትን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የመድን አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ሰምተናል።
ነገር ግን ቀድሞ የተጀመረውን እና አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርገው የማህበረሰብ አቀፍ መድህን አገልግሎት የገጠመው ችግር ከመሰረቱ ሊፈታ ይገባዋል። ይህንኑ እንዲመራ የተዘረጋውን ስረዓት ማዘመን እና የተሻለ ልምድ ካላቸው ሀገራት ልምድ መቀመሩ ግድ ይላል። ጦርነት ፣ ግጭት እና አለመረጋጋት ለአመታት የተፈታተናት ሀገር በእርግጥ ስርአት ያለው እና በመድህን የታገዘ የጤና አገልግሎቱን ፈር ብታስይዝ ለሌሎች ማህበራዊ ችግሮች የመፍትሄ መንገድ ማመላከቱ አይቀርምና ትኩረት ያግኝ መልዕክታችን ነው።
7ኛውን የናይል ሚዲያ ሽልማት በዲጅታል ሚዲያ ሚዘናዊ ዘገባ ዘርፍ ኢትዮጲያ አሸነፈች
የናይል ቤዜን የሚዲያ ሽልማት በየአመቱ የናይል ተፋሰስ ሃገራት እና የውሃ እና አካበቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች በኡጋንዳ የሚክሩበት መድረክ ነው፡፡ በመድረኩ ከሁሉም ሀገራት እና አለምዓቀፍ ተቋማት በቪክቶርያ ሃይቅ ዳርቻ ተገናኝተው የጥናታዊ ፅሁፍ ስራዎች ላይ ይወያያሉ፡፡ በመድረኩ ከ500 በላይ ምሁራን፣ አምባሳደሮች፣ የሀገራት መሪዎች እና ሚዲያዎች ይገኛሉ፡፡ እስከ 5 ቀን በሚፈጀው መድረክ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ፡፡ https://www.eventleaf.com/nbdf በዚህ መድረክ […]