በዶ/ር አለባቸው ፈንታው (+251 92 018 2921) ፣ እንጅባራ ዩኒቨርስቲ

በትዉፊት ላይ የበቀለ ጥበብ ፣ ኢ-ርቱእ የአዘፋፈን ስልትና በሁል-አቀፍ የጥበብ ካስማ የኢትዮጵያን ወግ ባህል አንግሳ በሌላ በኩል ደግሞ ወግ የለሽ ሰዉ መሆንንና የዘግቶ በላ ከንቱነትን ታወግዛለች፡፡ ጥበብን ለጥበብ ፣ ጥበብን ለሃገር ፣ ጥበብን ለትጋት ፣ ጥበብን ለታሪክ ፣ ጥበብን ለትግል ፤ ጥበብ ለማመስጠር ፣ ጥበብ ለመጠየቅ፣ ጥበብ ለመተንተን ፣ ጥበብ ጥበብ ሆኖ እውነት እንዲናገር ፣ ጥላቻን እንዲያከስም እንቁዋ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እድሜ ልኳን ታግላለች፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም አንድነትና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፆ አድርጋለች፡፡
የጥበብ ጉዳይ ሰው እንደመሆኑ መጠን ስለሰው ልጅ ክብርና ዋጋ በሚገባ አዚማለች፡፡ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በዓለም መድረክ አስተዋውቃለች፡፡ በኪናዊ ሀይል ማማለልና ወደ ቱባዉ ባህልና አኗኗር ቀዬ ይዞ መጓዝ እንደ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የተካነ ማን አለ?
የጥበቧ ንግስት አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ከአባቷ አቶ ሽባባዉ የኔአባት ከእናቷ ወ/ሮ ተናኘ ስዩም የመቻቻልና የመከባባር ተምሳሌት በሆነችዋ ከአገው ምድሯ የፍቅር ከተማ ቻግኒ ልዩ ስሟ ስጋዲ ሚካኤል ከምትባል ቦታ በ1966 ዓ.ም ተወለደች፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ፈርጀ-ብዙ አርቲስት ናት ፦ ድምፃዊት፣ ባለቅኔ፣ ተዋናይት፣ የዜማና የግጥም ደራሲ፣ ተዎዛዋዥና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች እንዲሁም ሰዓሊ ናት፡፡
እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በቻግኒ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርቷን እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ ተከታትላለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት እስከ ዳዊት ደርሳለች፡፡ በዝማሬም አሳልፋለች፡፡ ትምህርቷን በተሻለ ደረጃ ትማር ዘንድ ቤተሰቦቿ ወደ አዲስ አበባ ወሰዷት፡፡ ሆኖም ለሙዚቃ ካላት ከፍተኛ ፍላጎት አኳያ ወደ ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት መሄድ ታዘወትር ነበር፡፡
በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርት በተለይም ክራር፣ ኪቦርድና ጊታር መጫወትን ተምራለች፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ደግሞ በድምፃዊነት ሰርታለች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በኬኒያ ሲሆን ከኬኒያ ቆይታ መልስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ቤት በድምፃዊነት ተቀጥራ ሀገሯን አገልግላለች፡፡ ከታዋቂው አሜሪካዊ የሙዚቃ አቀናባሪ ቢል ላስዌል ጋር ትዳር መስርታ አንድ ወንድ ልጅ አፍርታለች ፡፡
እንቁዋ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የሙዚቃ ፍቅር ያደረባት ገና በልጅነቷ ነበር ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ አልበሞችን ሰርታለች፡፡
ፀሐይ በተሰኘውን አልበሟ ከሕዝብ ጋር ተዋወቀች፡፡ ከዛ በኋላ በሰራቻቸዉ አንድ ኢትዮጵያ፣ ጉራማይሌ፣ Abyssinia Infinite ፣ ሰምና ወርቅ እና ምስጋና በተሰኙ ስራዎቿ ዓለም-አቀፍ ዝናን አተረፈች፡፡
ኢትዮጵያ ሀገሬ የ3ሺህ ዓመት እመቤት የተሰኘው ስራዋ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡
‚የማንነቴ መለኪያ ኩራቴ መመኪያዬ ክብሬ የ3ሺህ ዓመት እመቤት አንድ ናት ኢትዮጵያ ሀገሬ እቴ አንች የእኔ ሙሽራ ሀገሬ እስኪ ልጠይቅሽ
ያገቡሻል ፣ ይፈቱሻል ፣ ያጩሻል አሁንም ድንግል ነሽ…‛
እያለች የኢትዮጵያን ሚስጥራዊነት፣ አንድነትና ሀያልነት ታሳያለች፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የእምቅ ሃብት ባለቤት መሆኗንና እኛም ሐብታችንን በስርዓት አለመጠቀማችንን ጭምር ትገልፃለች፡፡
‛እኔን የራበኝ ፍቅር ነው‛ በተሰኘው ዜማዋ በሀገራችን ሊከሰት የሚችለውን ችግር ቀድማ አሳይታናለች፡፡
‚… እስኪ ፈጠን ፈጠን እግር ተራመድ ምን ያኳትንሃል አመድ ለአመድ… የራበኝ እንጀራ ወይኑ መስሏቸው
የጠማኝ ወተቱ ወይ ጠጁ መስሏቸው …‛
እያለች ሀገራዊ ውክልና ባለዉ ዘይቤያዊ ሙዚቃዋ ኢትዮጵያ እንደምትታመም አሳይታለች፡፡ ሕዝብ በፍቅር ርሃብ እንደሚመታ አስቀድማ ስጋቷን ገልፃ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግሮች እንደሚጠላለፉ ፣ እንደሚዝሉና ከተራመዱም የሚራመዱት ወደአልተገባ ቦታ እንደሚሆን ተንብያ ነበር። ሕዝቧን ከ መ ዓ ት ለመታደግ በጥበብ አዋዝታ አስቀድማ አሳስባለች።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብሔር ወጀብ ሊመታት እንደሚቸል በጥበበ ቀንብባ ተንብያ ነበር። ‘’ጎጃም ያረሰውን ለጎንደር ካልሸጠ
ጎንደር ያረሰውን ለጎጃም ካልሸጠ የሽዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ…‘’
እያለች የኢትዮጵያ ሕዝብ መስተጋብር ሊታወክ እንደሚችል ከማንም ቀድማ ስጋቷን አስተጋብታ ነበር፡፡ ዘረኝነት ምን ያህል አስከፊና የዘመናችን ወረርሽኝ በሽታ እንደሆነ በይፋ በመኮነን የማታማታ ግን ይህ በሽታ በሰው ልጆች አንድነትና መተሳሰብ አማካኝነት መድሀኒት ሊገኝለት እንደሚችል
‘’ዘመን አመጣሽ የዘር በሽታ፤ መድሀኒት አለው የማታ ማታ …’’
ስትል እንደሚነጋ ያበሰረች ሲሆን የንጋቱ ብርሀን ደግሞ አንድነታችን መሆኑን እንዲህ ስትል ገልፃለች
“ስሩ እንዳይበጠስ መቋጠሪያው ደሙ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው ቀለሙ‛ …..
ይህ ሙዚቃዋን ወደር የለሽ የሚያሰኘው ችግርን ብቻ ሳይሆን መፍትሔውንም በኢትዮጵያዊነት ደም መግለፁ ነው፡፡
አድዋ በተሰኘዉ ሙዚቃዋ አባቶቻችን ህይወታቸውን ከፍለው ፋሽስቶችን አንኮታኩተው ለትውልድ ዝንታለማዊ ነፃነት አቀዳጁ የሚለው ዜማዋ ለሰው ሰው መከፈሉንና የኢትዮጵያዊነትን ጽናት ዋልታ አብጠርጥራ አሳይታለች፡፡
‚የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት‛…..
እኛ እኛን የሆንው ፡ ሰው የመሆን ክብርን ያገኘንው ሰው ተከፍሎ መሆኑንና ኢትዮጵያዊያን ስንተባበር ለጠላቶቻችን እቶን እንደምንሆን ያሳያል፡፡ የመተባበርን ሀያልነት ፣ የማይቻል መቻሉንና ከባርነት ይልቅ ሞት ራሱ ነፃነት መሆኑን በዚህ የጥበብ ትሩፋቷ አዉስታለች፡፡
እንቁዋ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ‘’አድዋ’’ በሚለው ስራዋ የአያቶቻችንን ድልና ጀብድ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለውና መጪው ትውልድ በድህነትና በዘረኝነት ላይ መዝመት እንዳለበት ‘’አድዋ ዛሬ ነው’’ በሚለው ስንኟ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡ በሺህ ገፅ መፅሐፍ ቢፃፍ ብዕርና ብራና የማይበቃዉን የአድዋ ድል ታሪክ በአንዲት ሙዚቃዋ በትውልድ ልብ ውስጥ አትማለች፡፡
ከጉባዔ ቃና፣ ከመንዙማና ከአሚናዎች የተፈለቀቀ ‘’የሰው ልጅ ክቡር’’ እያለች ባዜመችው ዜማዋ ከመንፈሳዊ አስተምሮ ባሻገር የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የከበረ ልዩ ፍጡር እንደሆነና የጦርነትን አስከፊነት በአለም መድረክ ላይ በስርቅርቅ ድምጿ መልዕክት አስተላልፋለች፡
ጂጂ የሀገሯን ገፅታ ከዳሰሰችባቸዉ ሙዚቃዎቿ መካከል ‘’አባይ’’ ተጠቃሹ ነዉ፡፡ ከአባይ ወንዝ መልካ- ምድራዊ ባህሪና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው ባሻገር ስለ ጥንታዊነቱም በንቡር- ጠቃሽና ሰዉኛ ዘይቤዎች አዚማለች፡፡ ስለ አባይ ወንዝ ከብሉይ ኪዳንና ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምራ እስከ ግብፅ አስዋን ግድብ ድረስ በዜማዋ ይዛን ከአባይ ጋር በየሸለቆው እንድንፈስ አድርጋናለች፡፡
‚የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት ….‛
የዚህ ዜማዋ ግጥም ብስለት የንቡር ጠቃሽ ዘይቤ አጠቃቀምና የፈጠራ ችሎታዋን ያመለክታል፡፡ ይህን ዘይቤ መጠቀሟ ሀሳቧንና ዜማዋን ጥልቅና ምጡቅ አድርጓቸዋል፡፡ በሰዉኛ ዘይቤዋ ደግሞ አባይ ሀገሩን ለምን እንደሚከዳ ትጠይቀዋለች ፡፡ የዜማዉ ቅኝት እንደ ዉሀዉ በልቦናችን እንዲፈስ ሆኖ የተሰራ መሆኑ ደግሞ እንዳይሰለች አድርጎታል።
በተጨማሪም ይህ ዜማዋ ኢትዮጵያ ሀብቷን በስርዓት ከተጠቀመችበት ከራሷ አልፋ ለሌሎች እንደምትተርፍ ያሳያል፡፡ አባይ ለሀገሩ ኢትዮጵያ እንደሚሆንም የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከመጣሉ ከ 10 ዓመት ቀድማ ተስፋዋን በዜማዋ ተንብያለች፡፡ ይህም እውን እየሆነ ነው፡፡
በሌላ በኩል አባይ አ በ ሳ እንደሚያመጣም በአጭሩ ገልፃ ነበር፡፡
‚አባይ አባይ አባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ ፡፡ ‚
አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ጥበብና ጥበበኛነት ከሕዝብ በፊት ቀድሞ ማሳየት፣ መምራት፣ መተንበይ፣መጠየቅ፣ማስጠንቀቅ፣መተቸትና ሲያስፈልግም ማሞገስ እንጅ እንደ ከብት ጭራ መከተል አለመሆኑን በተግባር አሳይታለች፡፡
ጂጂ በዚህ አላበቃችም
‘’ሞኔው ናታና አጎላጎሌ
እንፃይ ኩሊሲ ኮሬታ አሪሲ ናፈቀኝ ገጠሩ
የአባቴ በሬዎች ጃሪና ኮሎ በቀይ ጃኖ ተውበህ ናልኝ …’’
እያለች ለሙዚቃ ብቻ የተፈጠረ በሚመስለዉ ጉሮሮዋና መረዋ ድምጿ ባዜመቻቼዉ ሙዚቃዎቿ የአገውን ህዝብ ቋንቋ፤ታሪክ፣ ወግ፣ ባህል፣ ጥበብ፣ ትውፊት፣ አኗኗር እንዲሁም ህዝቡ ከተፈጥሮ ጋር ያለዉን መስተጋብር ለአለም ህዝብ ከማስተዋወቅ ባለፈ አገውነትንና የአገው ማንነትን ካለፈው፣ አሁን ካለውና ከሚመጣው ትውልድ ልብ ውስጥ በደማቅ ቀለም በመፃፍ የራሷን አይተኬ ሚና ተጫውታለች፡፡
በተለይም ጎሊማ በተሰኘው ሙዚቃዋ
ማርቆሱ ዳድ ብስስታጊ፣ ዳንግሊው ዳድ ብስስታጊ፣ ቻግኒው ዳድ ብስስታጊ፣
…..ካ ሳ ው ች ሰ አን ይ ው ስ ታ ጊ…….
እያለች በትጫዎተዉ ሙዚዋ ከተለያዩ ከተሞች ጋር የሚያገናኝ መንገድ አስፈላጊነት በአገውኛ ድንቅ ቅኔዋ አስተጋብታለች፡፡ ሁልጊዜም በሀገሯ የሐበሻ ልብስ መድረክ ላይ የምትገማሸረው ጂጂ ‘’እንፃይ ኩሊሲ ኮሬታ አሪሲ’’ በማለትም የአገውን ቀደምት የእርሻ ጥበብ ከማሳወቋ ባሻገር የአገውኛ ቋንቋ በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲዜምበት ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡
‘’ናፈቀኝ’’ በተሰኘው ሙዚቃዋ የአገው ምድርን መልከዓምድር፣ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት፣ የአገውን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነት፣ የቱሪስት መስህብ ስለሆነው የአርዲ ወንዝና ፏፏቴ ያዜመች የአገው ህዝብ ባለውለታዋ ጂጂ ከምትኖርበት ሀገር አሜሪካ ሁና ‘’ዛሬ በሰው ሀገር ትዝታው ገደለኝ እያለች’’ ቻግኒን አሁንም ሳትሰለች ደጋግማ ትጠራታለች፡፡
እዚህ ላይ የጂጂን ዓለም- አቀፍ ኮንሰርቶች ሳይጠቅሱ ማለፍ ንፉግነት ነዉ፡፡
የመጀመሪያ ኮንሰርቷን በኬኒያ አቀረበች። በፈረንሳይ በተዘጋጀው ዓለም–አቀፍ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ስራዎቿን አቅርባ ልዩ አድናቆትን አትርፋለች፡፡ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሎስ አንጀለስ ያቀረበችዉ ኮንሰርት ልዩ የሚያደርገዉ አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች የዉጭ ዜጎች ስለነበሩ ኢትዮጵያን በተለየ ሁኔታ ማስተዋዎቁ ነዉ፡፡
በስራዎቿ ረቂቅነትና ምጡቅነት እንደ ክሪስ ብላክዌል ያሉ ፕሮዲዩሰሮች እንደ ኸርበ ኸንኮክና ዋይን ሾርተር ያሉ የአሜሪካ የሙዚቃ ሊቃውንት ከፍተኛ እውቅና ያገኘች ሙዚቃዎቿንም ከእነዚህ ሊቃውንት ጋር አብራ የሰራችና ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ስልት የገባች አርቲስት ናት፡፡
በታዋቂዉ የሙዚቃ አቀናባሪና ፕሮዲዩሰር በሆነው Chris Black Well የተዋሀዱት የጂጂ ስራዎች በተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ተደጋግመው ቀርበዋል፡፡ በተለይ CNN, BBC, እና Aljazeera ስራዎቿን ደጋግመው በማቅረብ ለአለም ህዝብ አድርሰዋል፡፡ ለአብነት CNN፦ “እየፈነጠቀች ያለች የአፍሪካ ኮኮብ፡፡’’ ሲል አዎድሷታል፡፡
በተጨማሪም ቁጥር አንድ ተነባቢ ጋዜጦችና መፅሔቶችም የጂጂን ፎቶና የአልበሟን ርዕስ በፊት ገፃቸው ላይ በማተም በጥበብ የተካነች ድንቅ አርቲስት መሆኗን መስክረዋል፡፡
የጂጂን ስራ ለአለም የሙዚቃ ማህበረሰብ ካስተጋቡ ጋዜጦችና መፅሔቶች መካከል New Work Times ፣ CMJ እና Billboard ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡ እንዲሁም Glever እና Afro Pop Worldwide የጂጂን የጥብ ብቃት መስክረዋል ፡፡
የእጅጋየሁ ሽባባው ዘፈኖች ለተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ፊልሞች ማጀቢያ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ለአብነትም በሀገር ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለው ዘፈኗ ያልደረቀ ዕምባ ለተሰኘው ፊልም ማጀቢያነት ሲያገለግል Beyond Border በተሰኘውና አንጀሊና ጆሊ በተወነችበት አለም አቀፍ ፊልም ማጀቢያ በመሆኑ ተደማጭ ሆኗል፡፡
የጂጂ ሙዚቃዎች በአፍሪካ ህብረትና አለም አቀፍ የስብሰባ መድረኮችም የስብሰባ መልዕክት ማስተላለፊያ በመሆን ከፍ ብሎ ተስተጋብቷል፡፡
በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ሙዘቀኛ ብቻ ሳትሆን ባለቅኔ፣ ተዋናት፣ የዜማና የግጥም ደራሲ፣ ተዎዛዋዥና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችም ናት፡፡ ሴቶች በትወናው ዘርፍ ብዙም ጎልተው ባልወጡበት ዘመን ‘’የጊዜያችን ሰዎች’’ እና ‘’የሞት ፍቅር’’ በተሰኙ ፊልሞች በመተወን የትወና ብቃቷን በማሳየቷ ሽልማት ያሸነፈች አስደማሚ ተዋናይትም ናት፡፡
እኔም ስለጂጂ ትንሽ ብተነፍስ
ያሬድ ቀና ብሎ አንዴ ቢያዳምጥሽ ፣ ሞዛርት ከትቢያ ቤት ለአፍታ ቢሰማሽ ፣ ቤቶቨን ቢያዉቅማ ትንሽ ከጥበብሽ
ሌላ ምን ይሉሻል? “አንች ‘ኮ ክስተት ነሽ።‛
የሀሳብ ምጥቀት፣ የምናብ ጥልቀት ትንበያና መፍትሔ የመዝሙርና መንዙማ ቃና ያላቸው በነፍስ የተቃኙ ሙዚቃዎችን ስለኢትዮጵያ ያዜመች፣ የጥበብን መጠነ ርዕይ ገደብ አልባነት፣ ሁለንተናዊነትና ዝንተዓለማዊነት በቅጡ ያሳየች ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስተዋወቀች፣ ሀገሯን ያስቀደመች፣ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የተንቀለቀለች ድንቅ አርቲስት ናት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፡፡
ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ያስተዋወቀችና የኢትዮጵያን ሙዚቃ ዓለም–አቀፍ ያደረፈገች፣ ለእውነት ፣ ለሰላም ፣ ለአንድነት፣ለታሪክ ፣ ለፍቅር እና ለጀግንነት እንዲሁም ለሰው ልጅ ክብር የተጋች ከራሷ ይልቅ ሀገሯን ያስቀደመች የኢትዮጵያ ዓርማ እና የአፍሪካ ፈርጥ በመሆኗ ተገቢ እዉቅና ይሆናት ዘንድ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 352/2008 ዓ.ም በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት በማህበረሰብ አገልግሎት የዓመቱ የክብር ዶሬክትሬት (honoris causa ) ለእንቁዋ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እንዲሰጣት ወስኗል ፡፡ እንቁዋ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እንኳን ደስ አለሽ፡፡ Prepared by Alebachew Fentaw (PhD)
ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፤ እንጅባራ

ከሐምሌ 24-28/2015 በባህርዳር በሚካሄደው 'የዘወትሯ ኢትዮጵያ' የፎቶ ኤግዚቢሽን ላይ ይቀላቀሉ
ከሐምሌ 24-28 ባህር ዳር, ከነሃሴ 5-9 ድሬዳዋ, ከነሃሴ 16-20 ሐዋሳ, ከነሃሴ 25 -29 አዲስ አበባ በሚኖረን የዘወትሯ ኢትዮጵያ የፎቶ ኤግዚቢሽን ላይ በመገኘት ድንቅ የፎቶግራፍ ስብስቦችን ይመልከቱ! የዘወትሯ ኢትዮጵያን አብረን እንቃኝ – ግሩም ተሰጥኦ ባላቸው የፎቶ ባለሙያዎች የተቀነጨቡትን የማህበረሰባችንን ገጽታዎች ፍንትው አድርገው የሚያንጸባርቁ የፎቶግራፍ ስራዎችን በጋራ እንመልከት!We are coming to Bahirdar from July 31 to August […]