በታደለ አምበሉ

የካፒታል ገበያ እና አክሲዮን ገበያ ጥንስስ በኢትዮጲያ ተጀመረ የሚባለው በአፄ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ1960ዎቹ አካባቢ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ ፡፡ በ1963 አ፣ም የተመሠረተው የአዲስ አበባ የአክሲዮን ንግድ ማኅበር፣ ከግብጽ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛው እንደነበርም ይገነገርለታል፡፡
ያኔ በብሔራዊ ባንክ አደራጅነት የተመሠረተው ‹‹የአዲስ አበባ ሼር ዲሊንግ ግሩፕ›› በወቅቱ አገር በቀል የነበሩ የአክሲዮን ኩባንያዎች የአክሲዮን ይዞታቸውን በስፋት የሚሸጡበት ማዕከል ከመፍጠር በተጨማሪ፣ የተለያዩ የአክሲዮን ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎችንና ደረጃዎችን ማጎልበት መቻሉ ይነገራል፡፡
በተለይ የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱና አብዛኛው የግል ዘርፍ ተዋናዮች ከመክሰማቸው በፊት፣ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የሚባሉ ኩባንያዎች ሳይቀሩ ባለአክሲዮን እንደነበሩ የግማሽ ምእተ አመት ትውስታ ነው፡፡
ለአብነት እንደ አዲስ አበባ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቄራዎች ድርጀት፣ ጠርሙስ ፋብሪካ፣ ኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ፣ ኤችቪኤ ኢትዮጵያ፣ ተንዳሆ እርሻና ሌሎች እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 1974 ባለው ጊዜ ውስጥ አክሲዮን የሸጡ ኩባንያዎች እንደነበሩ ይገለጻል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ የግሉ ሴክተር በፍጥነት በማደግ ላይ የነበረ ሲሆን፣ ኩባንያዎችም አክሲዮኖችን ለሕዝብ በመሸጥ ካፒታል ያመነጩ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የአክሲዮን ገበያ የተጧጧፈ ሲሆን፣ የአክሲዮን ግዥና ሽያጭም የወቅቱ ጉልህ የንግድና የማኅበራዊ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ የወታደራዊው ደርግ ዘመን አብቅቶ በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን ይህ ጉዳይ ችላ ተብሎ የቆየ ሲሆን በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ እንድታደራጅ መወሰኑ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
የአክሲዮን ገበያ ተቋማዊ ሰርዓት የተበጀለት ፤ህዝብ የሚተማመንበት በመሆኑ በተለይ እንደ አሜሪካን እንግሊዝና ካናዳን የመሳሰሉ አገራት ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለአኮኖሚያቸው አጋዥ ሞተር ሆኖ አገልግሏል ማለት ይቻላል ፡፡
ከፍተኛ የካፒታል አቅም በመፍጠርም ለግሉ ዘርፍ ምጣኔ ሃብት የገንዘብ ፍሰትን በማሻሻል፣ በቀላሉ ወደ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል ሃብትን በመፍጠር ባለሃብቱና ባለድርሻው ትርፍም ሆነ ኪሳራቸውን በጋራ እንዲጋሩ የሚያደርግ ስርአት ነውና አዎንታዊ ተጽእኖ ያመጣል የሚል እምነት አለ፡፡
በተለይ የገንዘብ ጉድለት ወይንም እጥረት ላለባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ገንዘብ በመደልደል አገራዊ ሃብትን በማሳበሰብ ቀጥተኛ የውጭ ንግድን በመሳብ ለአገር ምጣኔ ሃብት እድገት ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ሁላችንም እንገነዘባለን።
ሀገራትም የአክሲዩን ገበያ ሲያቋቁሙ ቁጠባን በማስተዋወቅና በማበረታታት ለግለሰቦች አንደ አማራጭ የፋይናንስ መንገድ ይፈጥራሉ ፡፡
ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ለግሉ ዘርፍ የገንዘብ አቅርቦት ተደራሽነትን በማስፋት እና በኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ መጋራት የካፒታል ገበያ መኖር ወሳኝ ይሆናል ፡፡
መደበኛ የአክሲዮን ገበያዎች በተለያዩ አገራት ለሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵውያን ወደ አገራቸው መምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው፣ ትርፋማ በሆነና ደኅንነቱ በተጠበቀ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩበትን ዕድል የሚፈጥርላቸው ተመራጭ አሠራር ነው ፡፡
በዚህ ደረጃውን የጠበቀ መድረክ መጠቀማቸው ኢንቨስትመንታቸው በቀላሉ ወደ ጥሬ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል ንብረት (ሊኩዲቲ) እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ፣ በጊዜ ሒደትም አግባብነት ያለው የዋጋ ትመና እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡
ዳያስፖራው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ አገራት ባንኮች ውስጥ በቁጠባ መልክ ቢያስቀምጥም፣ ይህ ነው የሚባል ወለድ እያገኘበት እንዳልሆነ የምናየው ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ትርፋማ ሊያደርግ የሚችል የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠር ከተቻለ ግን፣ ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተው በአገራቸው ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ የዳያስፖራ ባለሀብቶችን መሳብ ይቻላል፡፡
በእርግጥ እንዲህ አይነቱ የአክሲዮን ገበያ ከመፈጠሩ በፊት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት የግድ ይላል ፡፡
በተለይም የሰለጠነ የሰው ሀይል በማብቃት ለአብነትም ኦዲተሮችን፣ የሂሳብ ባለሙያዎችን ፣የስቶክ ብሮከሮችን ፣የአክሲዮን ጠበቆችን ፣ የሚያሰልጥን ጠንካራ ተቋም ያስፈልገናል፡።
የፋይናንስ ገበያን ለመመስረት መሰረተ ልማት ላይ መዋለ ንዋይን በማፍሰስ ፣የፖሊሲ ለውጥ ማካሄድ የመሳሰሉ ስራዎችን መስራት የግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
እነዚህ ሁሉ የቤት ስራዎች ከተሰሩና የአክሲዩን ገበያን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ህግ ከወጣ መድረኩን ማዘጋጀት አስቸጋሪ አይደለም ፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ የንግዱ ህብረተሰብ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት ፡፡
በአጠቃላይ የካፒታል ገበያን ለመተግበር ኢትዮጵያ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተቋማቷን አሠራር ማሻሻል ይገባታል ፡፡ ከሁለት እጅ በላይ የሚሆነው የኢትጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ኢ-መደበኛ በመሆኑ ወደ መደበኛ ማምጣት፣ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን መቃኘት፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የተረጋጋ ዋጋ እንዲኖር ማድረግ እና ለኢንቨስተሮች በቂ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል ፡፡
በሀገሪቱ ያለው ንግድን ለማከናወን ያለው ከባቢ ሁኔታ (doing business environment) ስራዎች እየተሰራበት ቢሆንም አሁንም መሻሻል መቻል ይኖርበታል፡፡
እነዚህን ሁሉ ችግሮች ፈቶ ታሪክ ያስቀጥላል የተባለው የካፒታል ገበያ ተመስርቷል፡፡ የካፒታል ገበያውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ዶክተር ብሩክ ታዬ የሚመሩት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ግብይቱ የሚመራባቸውን ሕግጋት በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
የካፒታል ገበያውን ለማቋቋም ባለፈው ግንቦት 8 ቀን፣ 2015 አክሲዮን በይፋ መሸጥ ተጀምሯል። በገበያው መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል 25 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን የግሉ ዘርፍ 75 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል። የገበያውን የምሥረታ ሒደት የሚያስተባብሩት ዶክተር ጥላሁን እስማኤል እና ባልደረቦቻቸው ባለፉት ሣምንታት አዲስ በሚቋቋመው ገበያ እንዲሳተፉ ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር ምክክር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከፍተኛ የፕሮጀክት ማኔጀር የሆኑት ዶክተር ጥላሁን “ባንኮች የወደፊቱ የኢንቨስትመንት ባንክ እንደሚሆኑ፤ የወደፊቱ ሌላ ሁለተኛ ግብይቱን የሚያሳልጥ ተቋም እንደሚያቋቁሙ ነው የምንረዳው” ሲሉ አስረድተዋል።
ባንኮች “በተለይ በዕዳ ገበያ (fixed income securities) ቀጥተኛ ተሳታፊ ስለሚሆኑ ለእነሱ የሚጠቅም መሠረተ-ልማት ሆኖ ነው የሚመጣው። ስለዚህ እኛም ገለጻ ስናደርግ ከሌሎች የፋይናንስ ጥቅሞቹ ይልቅ መሠረተ-ልማትነቱን ተረድተውት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ነው የምንጠይቀው” የሚሉት ዶክተር ጥላሁን ከፋይናንስ ተቋማት “በጣም ከፍተኛ ፍላጎት” መኖሩን ታዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በ2016 ሥራ ሲጀምር የመንግሥት የግምዣ ቤት ሰነዶች ለሽያጭ ይቀርባሉ። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚገኙ የሚገኙ “እስከ አምስት የሚሆኑ ኩባንያዎች በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ገበያው ይገባሉ” ተብሎ እንደሚጠበቅ ዶክተር ጥላሁን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ባንኮችም በገበያው በመሳተፍ ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ካፒታል ያሰባስባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት መካከል ናቸው።
“በተለይ በፋይናንስ ዘርፍ የሚገኙ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ከካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የመጡትን መመሪያዎች ለማሟላት ብዙ የሚከብዳቸው አይደሉም” የሚሉት ዶክተር ጥላሁን “የፋይናንስ ሪፖርቶች ያወጣሉ፤ የኮርፖሬት አስተዳደራቸው ከሌሎች በተነጻጻሪ የተሻለ ነው። አክሲዮን ሽጦ የማስተዳደር ልምድ አላቸው። ስለዚህ እነሱን ወደ ገበያ ለማምጣት ከባድ ሆኖ አላገኘንውም” ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ገበያ በአሁኑ ወቅት 31 ባንኮች፣ 44 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ፣ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይገኛሉ። በተለይ ባንኮች ተጨማሪ ካፒታል ለማሰባሰብ ያላቸው ፍላጎት ወደ ኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ እንዲያመሩ ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል። “አሁን በባንክ ዘርፍ ያለው ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል ከ240 ቢሊዮን ብር አይበልጥም” የሚሉት የፕሮጀክት ማኔጀር በባንኮች የባለ አክሲዮኖች ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች “ከአራት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ብቻ ተጨማሪ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ” ፍላጎት እንዳለ የሚጠቁሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። በገበያው ከአንድ ሺሕ በላይ ኩባንያዎች በአክሲዮን ተቋቁመዋል። ዶክተር ጥላሁን እንደሚሉት ከእነዚህ ውስጥ 200 የሚሆኑት “በሰፊውም ባይሆን ሥርዓት ባለው መልኩ ለሕዝብ አክሲዮን” የሸጡ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን የመመሥረት ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት ባከናወኑት ጥናት በኢትዮጵያ “ከ400 ሺሕ በላይ ባለ አክሲዮኖች አሉ፤ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ አክሲዮኖች ገበያ ላይ ተሸጠዋል” የሚል መረጃ አግኝተዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት መደበኛ ባልሆነ መንገድ በተካሔደ የአክሲዮን ግብይት ሦስት ቢሊዮን ብር ከአንዱ ወደ ሌላው መዘዋወሩን በምሳሌነት የሚጠቅሱት ዶክተር ጥላሁን እስማኤል “ይኸ ሲደረግ አክሲዮን የሚሸጡ ተቋማት ወደ ገበያ ሲመጡ ምን አይነት መረጃዎች መስጠት እንዳለባቸው የሚቆጣጠራቸው እና የሚመራቸው ተቋም አልነበረም” ሲሉ ገበያው ያለበትን ጉድለት ያነሳሉ።
“ምን አይነት የፋይናንስ ሪፖርት፣ ምን አይነት ኦዲተር እንደሚጠቀሙም የሚደነግግ አልነበረም” የሚሉት ዶክተር ጥላሁን እንዲህ አይነቱ ግብይት በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ብቻ እንዲገደብ ምክንያት እንደሆነም እምነታቸው ነው። የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሲቋቋም ግን “የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢ የሆኑትን እንደ ብሮከር፣ ኦዲተር፣ ኢንቨስትመንት ባንክ የፋይናንስ እና የሼር አድቫይዘር” የመሳሰሉ ተሳታፊዎች በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ይገባሉ። አክሲዮኖቻቸውን ለሽያጭ የሚያቀርቡ ኩባንያዎች እና ተቋማት “ምን አይነት መረጃዎች” ለባለወረቶች ማቅረብ እንደሚገባቸው በመወሰን የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ሥርዓት እንዲበጅ የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ይወጣል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በገበያው ለሽያጭ የሚቀርቡ ሰነዶች እና አክሲዮኖች የማሻሻጥ ሥራውን ለሚያከናውኑ ግለሰቦች እና ተቋማት በመጪዎቹ ቀናት ፈቃድ መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ባለሥልጣኑ መደበኛ ባልሆነ መንገድ አክሲዮኖች የሚያሻሽጡ ደላሎችን ተገቢውን ሥልጠና እና ፈቃድ በመስጠት ወደ ግብይቱ የማስገባት ዕቅድ እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ብሩክ ታዬ ተናግረዋል።
ይኸን ውስብስብ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም ከሕግጋት እና ተቋማት በተጨማሪ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት ይሻል። የኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ እሸቱ እንደሚሉት የካፒታል ገበያው ሥራ ሲጀምር “ብዙ የተለያየ መልክ እና ባህሪ ያላቸው አክሲዮኖች ወደ ገበያው መግባት አለባቸው።” የግብይቱ ጠባይ ግን በወረቀት መልክ የሚታወቁትን የመዋዕለ-ንዋይ ሰነዶች እና አክሲዮኖች ሙሉ በሙሉ ይቀይራቸዋል። በወረቀት መልክ የሚታወቀው አክሲዮን ወደ ዲጂታል ቅርጽ ተቀይሮ በአንድ የሚከማችበት ሰንዱቅ (Central securities depositories) እንደሚያስፈልግ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
ለኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ከእንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች እና በርካታ ሕግጋት ባሻገር ግብይቱን የሚያመቻቹ ብቁ ባለሙያዎች ማዘጋጀት ያስፈልገዋል። ባለፉት ሣምንታት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ኢንቨስትመንት ባንኪንግ እና ካፒታል ገበያን በመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ሥልጠናዎች እየሰጠ ነው። ሥልጠናዎቹ እንደ ብሎምበርግ እና ዴሎይት ያሉ ኩባንያዎች ጭምር የሚሳተፉባቸው ናቸው።
በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ የምሥረታ ሒደት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርገውን ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት አቶ ኤርሚያስ “እዚህ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ባህሪያቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው [ተቀባይነት] ለዚህ ብዙ ቁመና እንዳላቸው መረጋገጥ አለበት። ለገበያው ሕግ ተገዢ እንዲሆኑ የተመሠከረላቸው ናቸው ብሎ ማመን አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን በተመለከተ የሚደረገው ውይይት፤ የሚዘጋጀው ሥልጠና በዋናነት አዲስ አበባ ላይ ያተኮረ ቢሆንም መሰል ገበያ በሌሎች አገሮች ያለውን ፋይዳ በተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አዎንታዊ አቀባበል ገጥሞታል። “የዚህ ሙያ ያላቸው በዚህ ኢንዱስትሪ፤ በፋይናንስ፣ በባንክ እና በኢንሹራንስ ዘርፍ ውስጥ ያሉ፤ በአገራችን አሉ የሚባሉ ኤኮኖሚስቶች የፋይናንስ ገበያ ተንታኞች፣ የሌላውን አገር የገበያ ስኬት እያዩ አይናቸው ሲጓጓ የነበረ ሁሉ በተቻለ መጠን ሕጉ በሚጠይቀው መንገድ ቅድመ ዝግጅት አድርገው ብቁ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተወዳዳሪም ሆኖ ለመገኘት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንዳሉ አውቃለሁ” ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል።
Antibiotic Resistance in Africa: Causes, Consequences, and the Growing Threat to Public Health
By Meselech Zelalem & Birhan Dejen (December 17, 2023) Antibiotic resistance (AMR) is a rapidly growing global health crisis, and Africa is one of the most vulnerable regions. With fragile healthcare systems, frequent misuse of antibiotics, and inadequate regulation, the continent is witnessing a surge in drug-resistant infections. As bacteria evolve to resist the effects […]