By NEBIYU Y. TEKLIE : አቶ አያሌው ተሰማ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሬዲዮ የማድመጥና ቴሌቪዥን የመከታተል ልምድ አላቸው፡፡ ቢሆንም ግን የሀገር ውስጥ የህዝብ የሚባሉ ሚዲያዎችን ብቻ አምነው አይከታተሉም፡፡ በከተማቸው የሚሰራጩ ሬዲዮ ጣቢያዎችን ሲያደምጡ ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ሲከታተሉ ሁሌም ጥያቄ የሚሆንባቸው ጉዳይ አለ፤ “ከተማው በተኩስ እየተናጠ ለምንድነው ስለጉዳዩ ትንፍሽ የማይሉት?”

የቅርብ ሩቆቹ የህዝብ ሚዲያዎች
የነቀምት ነዋሪዋ ወይዘሮ ትግስት በንቲ በአካባቢው የሚደመጡ ሬዲዮ ጣቢዎችም ሆነ የምትመለከታቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ በየለቱ ህዝብን ሥለሚያሸብሩ የጥይት ድምጾች ሲዘግቡ አላየችም፡፡
በመንግስትና በታጣቂዎች መካከል በሚደረግ የተኩስ ልውውጥ ከተማው ጦርሜዳ ሁኖ እነዚህ ሚዲያዎች ግን አንዳችም ነገር ስለጉዳዩ አይዘግቡም፡፡
ህዝቡ በዚህ አስጨናቂ ሰዓት ምን እንደተከሰተ አውቆ የራሱን ውሳኔ እንዲወስን ሚዲያዎች አንዳች የሙያና የተቋም ሀላፊነት አልተወጡም ትላለች ትግስት፡፡
በተመሳሳይ የጎንደሩ አቶ አያሌው ተሰማ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ለኛ ሩቅ ናቸው ይላሉ፡፡ አጠገባችን ሁነው የኛን ሀቅ መልሰው ካልነገሩን ምኑን የኛ ሆኑ ብለው ይጠይቃሉ፡፡
እንደርሳቸው አባባል የስልክ ኔትውርክ በተቋረጠበትና ብዙ ቤተሰቦቻቸው በሚኖሩበት ጋይንት የሚባል የገጠር አካባቢ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን የሰሙት ማታ ጠብቀው ከሚያደምጡት የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ነው፡፡
ግብር የሚከፍሉት መንግስት የሚያስተዳድረው ስሙን መጥቀስ ያልፈለጉት የህዝብ ሬዲዮ ጣቢያ ግን አድራሻው ከመኖሪያ ቤታቸው አጠገብ ነው፡፡
ሬዲዮ ጣቢያው ትኩሱን መረጃ በትክክል ካልነገረኝ ከመኖሪያቤቴ ውስጥ ቢሰራጭም ለኔ ቅርብ አይደለም፤ የቅርብ ሩቅ ዕንጂ ባይ ናቸው፡፡
በዝምታ ማለፍ
ለደህንነቱ ሲል ስሙንና የሚሰራበትን ተቋም መጥቀስ ያልፈለገው በመንግስት ሚዲያዎች የሚሰራ አንድ ጋዜጠኛ እንደነገረን በእደዚህ አይነት ሚደያዎች መስራት በተለይ በጦርነትና በቀውስ ጊዜ ጋዜጠኘነትህን እንድትጠላ ያደርግሃል ይላል፡፡
ሰው እየሞቱ፣ ሰው እየተፈናቀለ፣ ሰው እየተቸገ ስጉዳዩ ምንም አለመዘገብ የህሊና እዳ ነውና ሙያዊ ሃላፊነት አለመወጣት የህሊና ተጠያቂነትን አመጣብን ነው የሚለው፡፡
ለምሳሌ አንድ ታጣቂ ሀይል ከመንግስት ሀይል ጋር እየተዋጋ እያለ መንግስት በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ግድያ ቢፈጽም እንደጋዜጠኛ መዘገብ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሁኔታ አድለም የመንግስት ሀይልን ሰብአዊ ጥሰት ይቅርና፤ መንግስትና ታጣቂዎች እየተዋጉ መሆኑን እንኳ በድፍረት መዘገብ አትችልም ይላል ጋዜጠኛው፡፡
ደብረብርሃን ወይም ሻሸመኔ ከተሞች ውስጥ ያለና በህዝብ ግብር የሚተዳደር ሚዲያ ቢያንስ እዛው ከተማ ውስጥ የተፈጠረን ግጭት ወይ አለመረጋጋት በፍጥነትና በትክክል ዘግቦ ለህዝብ መረጃ አለማድረሱ ህዝቡን እንደመካድ የሚቆጥሩት አሉ፡፡
የአንድ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ የሆነውና ስሜን አትጥቀሱ ያለው ግለሰብ ለዚህ ተጠያቂው መንግስት ነው ይላል፡፡
ሚዲያዎች አንድን ጉዳይ ለመዘገብ ከመንግስት ይሁንታ ይጠብቃሉ ባይ ነው፡፡ በተለይ ወቅታዊና አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ደፍሮ እንዲዘገቡ ሃላፊነት የሚወስድ የሚዲያ አመራር እንደሌለ ይጠቅሳል፡፡
እያንዳንዱ ጉዳዮች የሚዘገቡት ከመንግስ ፍላጎት አኳያ ብቻ ታይተውና በፖለቲካ አመራሩ ሲፈቀዱ ብቻ ነው፡፡ በዚህም በዝምታ የሚታለፉ ወሳን ወቅታዊ ጉዳዮችና የህዝብ አጀንዳዎች በርካታ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ በአንድ አካባቢ የድሮን ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ንጹሃን ጉዳት ደርሶባቸው ከሆነ ጉዳዩ በመንግስት ሚደያዎች የሚዘገበው ለማስተባበልና የመንግስትን ጥፋት ለመከላል ነው፡፡ ጥቃቱ በተፈጸመበትና ጉዳት በደረሰበት ቀን ጉዳዩ የሚደያዎች ርዕስ አይሆንም፤ በዝምታ ይታለፋል፡፡
የውድቀት መንገድ
የጋዜጠኝነትና የኮሚኒኬሽን መምህሩ ዶ/ር አየለ አዲስ ግን አነጋሪ ጉዳይን በዝምታ ማለፍ ለሚዲያ የወድቀት መንገድ ነው ይላሉ፡፡
አሁን ያለንበት የዲጂታል ዓለም መረጃ በፍጥነትና በእያዳንዱ ሰው የሚሰራጭበት ዘመን መሆነን የሚጠቅሱት ምሁሩ፤ ሁሉም ሰው እጁ ላይ ባለው ስልክ መረጃ በሚያስተላልፍበት ዘመን ሚንስትሪም ሚዲያዎች የሚወዳደሩት ከዚህ እውነታ ጋር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
መረጃ የሚገኝበትና የሚተላፍበት አማራጭ ሰፊ በመሆኑ ሚዲያዎች ወሳኝ ጉዳዮችን በዝምታ ማለፋቸው የራሳቸውን ታማኝነትና ተወዳዳሪነት በመቀነስ የውድቀት መንገዳቸውን ያፋጥናል ባይ ናቸው፡፡
እኛ የምንለውን ብቻ ዘግቡ
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በተለምዶ የህዝብ የሚባሉ የመንግስ ሚደያዎች የመንግስን እቅድና ሃሳብ ብቻ መምራት ግዴታችሁ ነው ብሏል፡፡
በቅርቡ በተካደ አንድ የሚዲያ አመራሮች ስልጠና ላይ የተገኙት የኮሙኒኬሽ ሚንስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ ለሚዲያ አማራሮች በሰጡት የስራ አቅጣጫ “የሚከፍላችሁ መንግስት ነው፤ እናንተ የመንግስት ሰራተኞች ናችሁ፤ የመንግስትን ፖሊሲዎችና አፈጻጸሞች መተችትም አትችሉም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡”
ነጻ ያልወጡት የህዝብ ሚዲያዎች
የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ስልጣን እንደመጣ ሃሳብን በነጻት የመግለጽ መብትና እንዲከበርና ሚዲያዎች አንጻዊ ነጻነት እንዲኖራቸው በጎ እርምጃዎች ጀምሮ ነበር፡፡
አዲስ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2021ን በማውጣት ሚዲያዎችን መንግስት በጥብቅ ከሚቆጣጠር ይልቅ የርስበርስ ቁጥጥርን እንደሚያረታታም ገልጾ ነበር፡፡
‹‹የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚገዙበትን፣ የሙያ ሥነ ምግባርና የመልካም አሠራር ደንብ የሚያወጡበትን፣ የዘርፈን የሙያ ብቃት የሚያሳድጉበትን እና የተጠቃሚውን ህብረተሰብ ቅሬታዎች የሚያስተናግዱበትን አሰራር በመዘርጋት ራሳቸውን ለህዝቡ ተጠያቂ አድርገው እርስ በእርስ የሚተራረሙበት ሂደትን›› በግልጽ ፈቅዶ ነበር፡፡
ነገርግን መንግስት የኜ የሚላቸውን ሚዲያዎች የራሱን ሃሳብ ብቻ እንዲያስተላልፉ መቆጣጠርና መከታተል የጀመረው ወዲያው ነው፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን የመንግስተር አካሄድ በመተቸት ወቀሳ ሲሰዝሩ ይደመጣሉ፡፡ ኢዜማ ከአንድ አመት በፊት ባወጣው መግለጫ “መንግሥት ገለልተኛ ተቋማትን በገዢው ፓርቲ አባሎች ጠፍሮ በመያዝ ሚናቸውን እንዳይወጡ እና በሕግ አግባብ እንዳይሠሩ ማድረጉን ቀጥሏል ሲል ከሷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት እንድንወጣ እና የሀሳብ የበላይነት አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ የመገናኛ ብዙኀን ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በጽኑ እንደሚያምን በመግለጽ የመገናኛ ብዙሃን ከመንግስት ተጽኖ ነጻ ሁነው የሁሉንም ድምጽ ማሰማት አለባቸው ብሏል፡፡
ለመንግስት የበለጠ ጉልበት የሚሰጠው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ማሻሻያ
በቅርቡ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለማሻሻል ረቂቅ ህግ ይፋ መሆኑን ተከትሎ በርካታ የጠቃውሞ ድምጾች እየተሰሙ ነው፡፡
አስራ አራት የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ “አካሄድ እና የይዘት ግድፈቶች” እንደሚስተዋሉበት በመግለጽ፤ “በአዋጁ ከለላ ተሰጥቷቸው የነበሩ የቁጥጥር እና ሚዛን መጠበቂያዎች በረቂቅ አዋጁ ሊሻሩ የሚችሉ መሆናቸው በእጅጉ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ አባላት የሚመለመሉበት እና የሚሹመበት ሂደት ላይ ጉልህ የሚባል ማሻሻያ አድርጓል።
የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ወይም ተቀጣሪዎች የቦርዱ አባል እንዳይሆኑ የሚከለክለው የአዋጁ ድንጋጌ በማሻሻያው ተሰርዟል።
ከዚህ በተጨማሪም ማሻሻያው የቦርድ አባላት ምልመላ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት የሚያትተውን አንቀጽ ሰርዞታል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለስሥልጣን ዋና ዳይሬክተርን ሹመት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰጥቷል።
ይህም የህዝብ ጉዳዮችን በመንግስት አቅጣጫ በዝምታ በማለፍ በውድቀት መንገድ ላይ ላሉት ሚዲያዎች በጎ ዜና አይሆንም፡፡
በኢትዮጵያ የህዝብ የሚባሉ 51 ሬዲዮ ጣቢያዎች እና 28 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንደሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን መረጃ ያሳያል፡፡
የጋዜጠኞች አሰራር መመርያ: በርቀት ለማሰራጨት የበይነ መረብ መሳርያዎችን መጠቀም
Tips for Journalists Work ከርቀት ለማሰራጨት እንዲረዳኝ የበይነመረብ መሳርያ ስርአቶችን ለምን መጠቀም ያስፈልገኛል? የጊዜ እጥረትን ጨምሮ በገንዘብ ወይም የሎጂስቲክስ ምክንያቶች የራዲዮ ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ የሚያደርጉላቸውን ሰዎች በአካል ለማግኘት ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት አንድን ታሪክ በቦታው በመገኘት መዘገብ ወይም ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት መገናኘት ለጋዜጠኞች እና ለሌሎችም ከፍ ያለ አደጋ ሊኖረው ይችላል፡፡ ጥሩው ነገር […]