አዲስ አበባ — በደም ስር መጥበብና መዘጋት ምክንያት የሰውነት ክፍሎች የደም ዝውውር ሲያጡ ወደ “ጋንግሪን” የሚባል ከባድ የጤና ችግር ሊያመሩ እንደሚችሉ የጤና ባለሙያዎች አስጠነቀቁ። በተለይ በእጅና እግር ላይ የሚከሰተው ይህ ችግር በጊዜ ካልታወቀ ወደ አካል መቆረጥ ሊያደርስ ይችላል ተብሏል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምህርና የቀዶ ጥገና ሐኪም ፕሮፌሰር ነብዩ ስዩም እንደሚሉት፣ ጋንግሪን ማለት የደም ዝውውር ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሲቋረጥ የሰውነት ሴሎችና ቲሹዎች መሞት ነው። ኦክስጅንና አልሚ ምግቦች ወደ አካሉ ክፍል ሳይደርሱ ሲቀሩ ቆዳ፣ ጡንቻና ነርቮች በፍጥነት ይጎዳሉ።
ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የደም ስር መዘጋት በልብ ላይ ሲከሰት የልብ ድካም፣ በአንጎል ላይ ሲከሰት ስትሮክ፣ በእግር ወይም በእጅ ላይ ሲከሰት ደግሞ ጋንግሪን ያስከትላል።
የጋንግሪን ዋና መንስኤዎች
በድንገት የሚከሰቱ የጋንግሪን አይነቶች በአብዛኛው በደም መርጋት ምክንያት እንደሚመጡ ተገልጿል። የረጋ ደም ከልብ ተነስቶ ወደ እግር ወይም ወደ እጅ የሚሄዱ የደም ስሮችን ሲዘጋ ከዚያ በታች ያለው የሰውነት ክፍል የደም እጥረት ያጋጥመዋል።
በሌላ በኩል ቀስ እያለ የሚመጣው የደም ስር መጥበብ በብዛት ከስኳር በሽታ፣ ከደም ግፊት፣ ከከፍተኛ ኮሌስትሮልና ከሲጋራ ማጨስ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተነግሯል። እነዚህ ሁኔታዎች በደም ስሮች ውስጥ የስብ ክምችት እንዲፈጠር በማድረግ የደም ፍሰቱን ይቀንሳሉ።
በኢትዮጵያ በተለይ ያልታወቀ ወይም በአግባቡ ያልታከመ የስኳር በሽታ ለጋንግሪንና ለእግር መቆረጥ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ሐኪሞች ያስጠነቅቃሉ።
ቀድሞ የሚታዩ ምልክቶች
ባለሙያዎች እንደሚሉት ጋንግሪን ከመከሰቱ በፊት ሰውነት በርካታ ማሳሰቢያ ምልክቶችን ያሳያል። ከእነዚህ መካከል፦
- እግር ወይም እጅ መደንዘዝ
- የቆዳ ቀለም መቀየር
- እግር መቅላት ወይም መንጣት
- የእግር ፀጉር መርገፍ
- ጥፍር መፈርፈር
- ቆዳ ማብለጭለጭ
- ቁስለት መፈጠር
- እግርን ማንቀሳቀስ መቸገር
በድንገት የሚከሰት የደም ስር መዘጋት ከባድ ህመም፣ የቀለም ለውጥና የንክኪ ስሜት መጥፋትን ሊያስከትል ይችላል። በዚህ ደረጃ ሕክምና ካልተደረገ የተጎዳውን አካል ማስወገድ ሊያስፈልግ ይችላል።
የሕክምና እና መከላከል መንገዶች
ሐኪሞች እንደሚመክሩት፣ የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊትና ኮሌስትሮልን በትክክል መቆጣጠር የጋንግሪን አደጋን በእጅጉ ይቀንሳል። ሲጋራ ማጨስን ማቆም፣ መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግና ወቅታዊ የጤና ምርመራ ማድረግም አስፈላጊ ነው።
ከ40 ዓመት በላይ ያሉ ወይም የስኳር፣ የደም ግፊትና የኮሌስትሮል ችግር ያለባቸው ሰዎች በሳምንት ቢያንስ 4 እስከ 5 ቀን ለ40 ደቂቃ ወይም ከዚያ በላይ የአካል እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ተመክሯል።
እንዲሁም ደም እንዳይረጋ የሚከላከሉ መድኃኒቶች፣ እንደ አስፕሪን እና ኮሌስትሮል የሚቀንሱ ስታቲን መድኃኒቶች በሐኪም ምክር መውሰድ የልብ ድካምን፣ ስትሮክንና ጋንግሪንን ለመከላከል ጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።
ባለሙያዎች በመጨረሻ እንደሚያሳስቡት፣ በእግር ወይም በእጅ ላይ የቀለም ለውጥ፣ መደንዘዝ፣ ቁስለት ወይም ያልተለመደ ህመም ከታየ በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ከባድ አደጋን ሊከላከል ይችላል።

Is Ethiopia’s $2.49 Billion Steel Backbone a Gateway to Growth or a Trap of Corrosive Capital?
By Ayele Addis & Team The Grand Ambition: A Steel Corridor to the Sea At dawn on the outskirts of Addis Ababa, inside a maintenance compound lined with imported Chinese electrical panels, Ethiopian technicians begin the grueling work of keeping one of Africa’s most ambitious transport systems alive. These engineers inspect the braking and signaling […]