By Eshetu Geletu ጥቂት ስለኢትዮጵያ ሬዲዮው ዜና ፋይል
ዜና ፋይል በጋሽ ጌታቸው ሀ/ማርያም አማካይነት በ1979 ተጀመረ፡፡ ጋሽ ዳሪዎስ ሞዲ _ ጋሽ ጥላሁን በላይ _ ነጋሽ መሀመድ _ ዋጋዬ በቀለ _ ብርትኩዋን ሀ/ወይን እና እሸቱ ገለቱ እስከ 1997 ድረስ በቅደም ተከተል ዜና ፋይልን የመሩ ሙያተኞች ናቸው፡፡ በዜና ፋይል ክፍሉ እያንዳንዱ ጋዜጠኛ የራሱን የአጻጻፍና የአቀራረብ ቀለምን ይዞ አጠቃላይ ህብራዊ ጣዕሙም የሲንፎኒ ኦርኬስትራ ያህል ሁሉም ከዋናው ቅኝት ጋር በጋራ የተዋደደ እና የተሰናሰለ እንደነበር ባለታሪኩ ይመሰክራል፡፡
የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይልን ዛሬም ድረስ የማይዘነጋ ያደረገው በባለታሪኩ እምነት እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ሁሌም በእውቀትና ልምድ ራሱን ማዳበሩ ፣ እርስ በርስ የሞቀ ፉክክር የመኖሩን ያህል ከአንድ የስራ ቡድንነት ባለፈ እንደ አንድ ቤተሰብ ስራውን ማናበብ መቻሉ ፣ ለሆነ ሰው ታይታ ሳይሆን አለቃ ኖረ አልኖረ ሁሉም ስራውን ለይቶ አክብሮ መስራቱ ፣ ከአንጋፋው እስከ ጀማሪው ጋዜጠኛ ድረስ አብሮ መስራቱ በትውልድ ቅብብሎሽ የሙያ ልምዳቸውን ይበልጥ እንዲሻሻል እድል ይፈጥራል፡፡
በብዙ ታዳሚዎች ዘንድ አይረሴ ሆኖ ስለቀጠለው ዜና ፋይል እሸቱ ሲናገር ከጀማሪዎቹ እስከ ነባርና አንጋፋዎቹ ድረስ ያሉትን በትውልድ ቅብብሎሽ የካበተ እውቀትና ልምድ ባለቤቶችን አሰባስቦ ከመያዙ ባሻገር በጋዜጠኞቹ መካከል ፉክክርም በጋራ መናበብም ያለበት ሆኖ ስለዝግጅት ጥራትና የአድማጮች እርካታ መጨነቅ ጎልቶ የሚታይበት የተግባራዊ ጋዜጠኝነት ሙያ መቅሰሚያና ማዳበሪያ አምባ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ጋዜጠኞች እንደተቀጠሩ የሚወስዱትን ስልጠናዎችን ተከትሎ በአፈጻጸማቸው ውጤት መሰረት እንደ ችሎታቸውና የአቀራረብ ድምጻቸው ታይቶ በየዝንባሌያቸው ነው የሚመደቡት፡፡ አዲስ ገቢዎቹ በነባርና አንጋፋዎቹ እየተመሩ ለስምሪት በተከታታይ አጅበው በመውጣት የመረጃ አሰባሰብን እንዲለማመዱ ፣ በስቱዲዮ ደግሞ ድምጹን እንዲሞርዱድ እና በቢሮም በየሰአቱ በሞኒተሪንግ የሚቀረጹ የውጭ ዜናዎችን በፍጥነት የመተርጎም ስራን ማከናወን ስለመቻላቸው ሲረጋገጥ ከወራት ክትትል ወዲያም የጋዜጦች አምድ ዝግጅትን እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡
የመስክ ስምሪትን በራሳቸው ወጥተው እንዲሸፍኑና የዋና የምሽት 2 ሰአት ዜና ዝርዝርን ለማንበብ ብቁ አእስኪሆኑ የቅርብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይቆያሉ፡፡ በዚህ የልምምድ ወቅት አዲስ ዘጋቢዎቹ ረቂቅ ዜናዎችን ቢሰሩም የማይተላለፍ ሆኖ ነባሮቹ ከዘገቡት ጋር በአንክሮ በማመሳከር ድክመታቸውን በመለየት ረቂቃቸውን እያረሙ እንዲማሩበት ይደረጋል፡፡
በብዙ መልኩ ባለታሪኩ እሸቱ በጋዜጠኝነት ሙያ እንደ አብነቴ ነው ብሎ ከሚያወሳው ነጋሽ መሀመድ ክህሎት መካከል ዜና አጻጻፍና አቀራረብን የረቀቀ ጥበብ ያህል አክብሮት እስከመጨረሻዋ የስቱዲዮ ቀረፃ ደቂቃ ድረስ ተጨንቆ የቃላት ሀብታምነቱን በሚያሳብቅ መልኩ ቃላት እየቀያየረና ንበቱን እየሞረደ በአርትኦት እያሸ የሚዘልቅበትን ትዕግስቱን ያደንቅለታል፡፡
የባልደረባው አለምነህ ዋሴ ለስሜት ቅርብ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም በአድማጭ ዘንድ የድምጽ ቀለምን (Audio color) የሚያሳይ ምስል ለመከሰት የሚሄድበት ርቀትና ትልቅ አነጋጋሪ ጉዳይ ሲከሰትና የህዝብ ትኩረት አርፎበታል ብሎ የሚገምተውን ዜና ወስዶ ቀድሞ አድማጭን በአቀራረብ ለመማረክ ታሳቢ አድርጎ የሚያሳየው እሽቅድምድም የሙያ ጉጉቱን ስለሚያመለክት ባለታሪኩ የሚወድለት ባህሪው ነው፡፡
በአጫጭር አረፍተ ነገሮቿ የዜናውን ጭብጥ ቀለል አድርጋ ልክ አጠገብ ሆና እንደ ወግ እያወራች ያህል እንዲሰማን የምታደርገው ንግስት ሰልፉ ደግሞ ሌላዋ ልዩ የዜና ፋይል ቀለምነቷን እሸቱ በትዝታ ያወሳዋል፡፡ ብርቱካን ሀ/ወይን ደግሞ በዜና አነባበብ ለመደመጥ ጉልበታም (Authoritative) የሆነ የቆፈጠነ የአድማጭን ቀልብ የሚገዛ አይነት ድምጽ የተቸራት ድንቅ መሪ ዜና አቅራቢ (Anchor Person) በመሆን ሌላው የክፍሉ ልዩ ጌጥ ሆና ዘልቃለች፡፡
የክፍሉ ኃላፊ ከነበረው ጋሽ ዳሪዎስ ሞዲ ደግሞ የውጭ ዜናዎችን ትርጉም በተለይም እጅግ ውስብስብ ለሆኑ የእንግሊዝኛ ቃላት ጭምር በገላጭ የአማርኛ አቻ ቃላት በፍጥነት የሚተረጉምበትንና አለም በዚህ ሳምንት ሲዘጋጅም ስለቅንብሩ ውበት በመመሰጥ እሸቱ ለሚያቀርበው አቅጣጫ በመስጠት እንዲዘጋጅ የሚያደርግበት መንገድ ስለቅንብር ምሳሌው አድርጎ ባለታሪኩ ያነሳዋል፡፡ ሌላው ዝምተኛ ጀግና ብሎ የሚያስታውሳቸው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ማዕከል ኃላፊ ከነበሩት አቶ ጥላሁን በላይ ደግሞ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በጥሞና የማስተዋል ልምድን ከመቅሰም ባሻገር የመጽሀፍ ንባብ ባህልን ማዳበር እንደሚያስፈልግና በተለይ ፖለቲካዊና አለም አቀፍ ግንኙነት ላያ ያተኮሩ መጽሀፍትን ያውሱት ስለነበር ለፕሮግራም ዝግጅት ግብአት በማከል አስተዋጿቸው የጎላ እንደነበር ባለታሪኩ ማስታወስ ይሻል፡፡
የትርጉም አቻ ቃላትንና የቃለ ምልልስ ጥያቄዎችን ለማውጣት እርስ በርስ አየተነጋገሩ በመዋጮ ይዘቱን ለማዳበር የሚደረገው መልካም ተሞክሮ እንዲሁም የስፓኒሽ ፣ የሩሲያ ፣ የአረብኛ ፣ የፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን ቢያንስ የሚሞክሩ ስለነበሩ በዜና ዝግጅት ወቅት የስምና ቦታ መጠሪያዎችን በተሻለ የማቅረቡ እድል ለሬዲዮው ተደማጭነት የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው ባለታሪኩ ያምናል፡፡
ዜና ፋይል ውስጥ በቀን ሁለቴ የሚከወነው በኤዲቶሪያል ፖሊሲ ላይ የተመሰረተው የኤዲቶሪያል ስብሰባ አሰራሩን ሁሉም እንዲረዳው በማድረጉ ሰራተኛው የዜና እወጃውን ሰአት አለቃው አድርጎ ስለሚያስብ አላግባብ መጠባበቅ ሳይኖር በተዘረጋው ስርአት መሰረት ቀድመው የደረሱ ጋዜጠኞች ዜናውን በሰአቱ ለማድረስ ተረባርበው የሚሰሩበት ባህል በመዳበሩ ችግር ሲያጋጥም ተተካክቶና በምክክርም ተሸፋፍኖ በጋራ የመስራት ልምዱ ለውጤታማነቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡
በዜና ፋይል ውስጥ በመደበኛነት በመስክ ስምሪት የሚሸፈኑ የሀገር ውስጥ ዜና ዘገባን ከማዘጋጀትና የውጭ ዜናዎችን ለሬዲዮ በሚስማማ ከመተርጎምና ያልተገለጡ አነጋጋሪ የህብረተሰብ ጉዳዮች ላይ የምርመራ አሳሽ የክትትል ዘገቦችንና ዜና ትንታኔዎችን ከማጠናቀር አንስቶ ባለታሪኩ ለአብነት ሀገራዊ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎችን አሰራር የሚፈትሹና አለም አቀፋዊ ሁነቶች ላይ ያጠነጠኑ የትኩረት ጉዳዮችን የሚያብራሩ የወቅታዊ ሪፖርት ዜና ፕሮግራሞችን ጭምር በይዘት ፣ በጥልቀት ፣ በንበት እና በአቀራረብ ረገድ አድማጭን በሚገዛ መልኩ በልዩነት ከሚያቀርቡት መካከል አንዱ ነበር፡፡
በዘመኑ በህብረተሰብ ዘንድ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረውን ዘወትር ዓርብ ከቀኑ 5፡30 አንስቶ ለ20 ደቂቃ ሲተላለፍ የቆየው ሰፊ ዳሰሳዊ ጥልቅ ዝርዝር የትንተና ሚኒ ዶክመንተሪ የአቀራረብ ቅርፅን (ዘይቤን) የሚከተለውን “የሰሞኑ ታላቅ ዜና” የተሰኘውን ቅንብር ከይዘት ቀረፃና ከፕሮግራም ቲም መረጣ አንስቶ በ1988 ዓ.ም ወርሀ መጋቢት ላይ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ “በባልካን ቀውስ” ላይ ያተኮረ የበኩር ትንተናዊ ጥንቅርን ከማቅረብ አንስቶ በተከታታይም ግንባር ቀደም አዘጋጅ በመሆን የፕሮግራሙን ከፍታ በማስጠበቅ ረገድ ባለታሪኩ ከፍተኛ ድርሻው አይዘነጋም፡፡
ርዕሰ ጉዳይን አንስቶ በጋራ በጥልቀት የመወያየት ባህል የጎለበተበት መሆኑ ፣ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎችን የሚያውቁ ብሎም አብዛኛውን ድፍን ኢትዮጵያንና የውጭ ሀገራትን ዞረው ያዩ ሙያተኞችን በቡድኑ ማካተቱ ፣ አባላትን በተቻለ መጠን ከፖለቲካ አድሎ ይልቅ ለሙያው የማደርና እርስ በርስ የመተራረም ልምድ መጎልበቱ እና ስለሙያ ጥራት ጠንቅቀው አውቀው ለትርጉምና ለአርትኦት ብቻ በሚል ጭምር ዜና የማያነቡ ግን ዜናን በልዩ የሚያዘጋጁ መኖራቸው ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳል፡፡
ባለታሪኩ እሸቱ ገለቱ አብሮአቸው ከሰሩት ጋዜጠኞች መካከል በቃሉ ደገፋው _ ዳንኤል ወ/ሚካኤል _ ገነት አስማረ _ ዋጋዬ በቀለ _ አማረ መላኩ _ ተስፋዬ መክብብ _ ተፈሪ አንለይ _ ተፈሪ ለገሰ _ ቴዎድሮስ ነዋይ _ ሺበሺ ፀጋዬ _ ዘመድኩን ተክሌ _ የኔነህ ከበደ _ ስለሺ ሽብሩ _ ደግነህ ገ/ስላሴ _ ብሩክ ነጋሽ _ አዲስ ለማ _ እሸቱ አበራ _ እሸቱ አለሙ _ ቢንያም ከበደ _ አብዲልሰመድ መሀመድ _ በላይ በቀለ _ እያደር አዲስ _ ለምለም በቀለ _ አለማየሁ ግርማ _ ሙላቱ አለማየሁ _ ጌታሁን ንጋቱ _ ዳንኤል አማረ _ ሲሳይ ዘሪሁን _ ሳሙኤል ፍቅሬ _ ሰለሞን ግዛው _ ነፃነት ፈለቀ _ አሸናፊ ሊጋባ እና ሰኢድ ሙሄ ናቸው፡፡
ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዜና ፋይል ጋዜጠኛው የአመት እረፍት ሁሉ ወጥቶ ተጨክኖ የማይቀርበት ክፍል የመሆኑ ምክንያት በተለይ ቅዳሜና እሁድ ቢሮው እንዳይቀዛቀዝ ሻይ ቡና ተፈልቶ በቡና ቁርስ ታጅቦ በደራ ጨዋታና ቀልድ የሚደምቅበት ነው የሚለው ባለታሪኩ በጋዜጠኞቹ ፣ ጸሀፊዎቹና የሞኒተሪንግ ሰራተኞቹ መካከል የቤተሰብ ያህል ቅርርቡ እጅግ የሚያስቀና ነበር ይለናል፡፡

(Who are in the photo: top left to right- Negash Mohammed & Nigist Selfu. Bottom left to right- Alemneh Wasse, Birtukan H/ Wein & Eshetu Geletu)
‘የኢትዮጵያ ሬዲዮ’ ጣቢያ 90 ዓመታትን በትጋት ለኢትዮጵያ! በኢትዮጵያ የአሁኑን
‘የኢትዮጵያ ሬዲዮ’ ጣቢያ ለማቋቋም ስራ ሲጀመር ዘርፉ በአለም ላይ ገና ለጋ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የሬዲዮ ስርጭት ስትጀምር አሁን ላይ ስመጥር የሆኑ፤ ያኔ ግን ገና ያልተመሰረቱ ሀገራት ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ ዉጭ መላዉ አፍሪካ በቅኝ ግዛት እየማቀቀም ነበር፡፡ የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለአለም ገና እንግዳ በነበረበት በዚያ ወቅት ታዲያ የኢትዮጵያ ሬዲዮ በአየሩ ላይ መናኘት ጀምሯል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ስርጭት […]